Thursday, February 18, 2010

መጽሐፈ ኢዮብ 1

ምዕራፍ 1።

1፤ ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ።

2፤ ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር።

3፤ ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ።

4፤ ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር።

5፤ የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ። ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር።

6፤ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ።

7፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።

8፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው።

9፤ ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት። በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?

10፤ እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል።

11፤ ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።

12፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።

13፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር።

14፤ መልክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ። በሬዎች እርሻ ያርሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ይሰማሩ ነበር፤

15፤ የሳባም ሰዎች አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።

16፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎቹንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችንም በላች፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።

17፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ከለዳውያን በሦስት ረድፍ ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።

18፤ እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤

19፤ እነሆም፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፥ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፥ ሞቱም፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።

20፤ ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤

21፤ እንዲህም አለ። ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን።

22፤ በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።

መጽሐፈ ኢዮብ 2

ምዕራፍ 2።

1፤ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ።

2፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።

3፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፤ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል።

4፤ ሰይጣንም መልሶ እግዚአብሔርን። ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል።

5፤ ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው።

6፤ እግዚአብሔም ሰይጣንን። ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው።

7፤ ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው።

8፤ ሥጋውንም ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።

9፤ ሚስቱም። እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው።

(የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው)

ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፥ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች።

10፤ እርሱ ግን አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።

11፤ ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፤ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው በልዳዶስ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ።

12፤ ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፤ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ።

13፤ ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፤ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተዋልና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።

መጽሐፈ ኢዮብ 3

ምዕራፍ 3።

1፤ ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ።

2፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህ አለ።


3፤ ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥

ያም። ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት።


4፤ ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤

እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥

ብርሃንም አይብራበት።


5፤ ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፤

ዳመናም ይረፍበት፤

የቀን ጨለማ ሁሉ ያስፈራው።


6፤ ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፤

በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤

በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።


7፤ እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፤

እልልታ አይግባበት።


8፤ ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ

ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት።


9፤ አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤

ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥

የንጋትንም ቅንድብ አይይ፤


10፤ የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥

መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።


11፤ በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም?

ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም?


12፤ ጕልበቶች ስለ ምን ተቀበሉኝ?

ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ?


13፤ አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤

አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤


14፤ የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት

ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥


15፤ ወይም ቤታቸውን ብር ከሞሉ

ወርቅም ካላቸው መኳንንት ጋር፥


16፤ ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፥

ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።


17፤ ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፤

በዚያም ደካሞች ያርፋሉ።


18፤ በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፤

የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።


19፤ ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፤

ባሪያም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።


20፤ በመከራ ላሉት ብርሃን፥

ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥


21፤ የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ

ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥


22፤ መቃብርን ባገኙ ጊዜ

በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ

ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?


23፤ መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥

እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው

ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ?


24፤ ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥

ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።


25፤ የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥

የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።


26፤ ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፤

ነገር ግን መከራ መጣብኝ።

መጽሐፈ ኢዮብ 4

ምዕራፍ 4።

1፤ ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።


2፤ አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀየማለህን?

ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው?


3፤ እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥

የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥


4፤ ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥

አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።


5፤ አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፤

ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ።


6፤ አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥

የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን?


7፤ እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው?

ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?


8፤ እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥

መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።


9፤ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥

በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።


10፤ የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥

የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ።


11፤ አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥

የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ።


12፤ ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥

ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች።


13፤ በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥

የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥


14፤ አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ

ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ።


15፤ መንፈስም በፊቴ አለፈ፤

የሥጋዬ ጠጕር ቆመ።


16፤ እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥

ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤

የዝምታ ድምፅ ሰማሁ።


17፤ በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥

ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን?


18፤ እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፤

መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤


19፤ ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥

መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥

ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?


20፤ በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤

ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ።


21፤ ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን?

አለጥበብም ይሞታሉ።

መጽሐፈ ኢዮብ 5

ምዕራፍ 5።

1፤ አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን?

ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?


2፤ ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥

ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።


3፤ ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥

ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።


4፤ ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥

በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥

የሚታደጋቸውም የለም።


5፤ የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥

ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤

የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።


6፤ ችግር ከትቢያ አይመጣም፥

መከራም ከመሬት አይበቅልም፤


7፤ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥

ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።


8፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥

ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።


9፤ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና

የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።


10፤ በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥

በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።


11፤ የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥

ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።


12፤ እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም

የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።


13፤ ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤

የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።


14፤ በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥

በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።


15፤ ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ

ከኃያሉም እጅ ያድነዋል።


16፤ ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤

ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።


17፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤

ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።


18፤ እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤

ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።


19፤ በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥

በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።


20፤ በራብ ጊዜ ከሞት፥

በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።


21፤ ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤

ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።


22፤ በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤

ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤


23፤ ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤

የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።


24፤ ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤

በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።


25፤ ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥

ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።


26፤ በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥

በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።


27፤ እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤

አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።

መጽሐፈ ኢዮብ 6

ምዕራፍ 6።

1፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።


2፤ ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ!

መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ!


3፤ ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤

ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል።


4፤ ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥

መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤

የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል።


5፤ በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን?

ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን?


6፤ የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን?

ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን?


7፤ ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤

እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።


8፤ ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ!

እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!


9፤ እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ

እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!


10፤ መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤

በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥

የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።


11፤ እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው?

እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው?


12፤ ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን?

ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?


13፤ በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ

ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?


14፤ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት

ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ

ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።


15፤ ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥

እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።


16፤ ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥

አመዳይም ተሰወረባቸው፤


17፤ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤

በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።


18፤ በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤

ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።


19፤ የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥

የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።


20፤ ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤

ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።


21፤ አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤

መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።


22፤ በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤

ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤


23፤ ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤

ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?


24፤ አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤

የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።


25፤ የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው!

የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?


26፤ ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና

ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?


27፤ በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤

ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ።


28፤ አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤

በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።


29፤ እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤

ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።


30፤ በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን?

አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?

መጽሐፈ ኢዮብ 7

ምዕራፍ 7።


1፤ በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?

ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን?


2፤ አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥

ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥


3፤ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥

የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ።


4፤ በተኛሁ ጊዜ። መቼ እነሣለሁ? እላለሁ።

ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥

እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ።


5፤ ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፤

ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል።


6፤ ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥

ያለ ተስፋም ያልቃል።


7፤ ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፤

ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።


8፤ የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፤

ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም።


9፤ ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥

እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም።


10፤ ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥

ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።


11፤ ስለዚህም አፌን አልከለክልም፤

በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፤

በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ።


12፤ ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥

እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን?


13፤ እኔም። አልጋዬ ያጽናናኛል፥

መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥


14፤ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥

በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤


15፤ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ

መታነቅንና ሞትን መረጠች።


16፤ ሕይወቴን ናቅኋት፤ ለዘላለም ልኖር አልወድድም።

የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ።


17፤ ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥

ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥


18፤ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥

ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ?


19፤ የማትተወኝ እስከ መቼ ነው?

ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው?


20፤ ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ?

ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ?

ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ?


21፤ ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም?

ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም?

አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤

ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።